በዳንኤል ክብረት: -
ክፍል አንድ
1.1 አጠቃላይ የግእዝ ሥነ ጽሑፋዊ ሀብት
የግእዝ ቋንቋ ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ጊዜ ያስቆጠረ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ያለው ቋንቋ ነው፡፡ እስካሁን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የግእዝ ሥነ ጽሑፍ በተጻፉበት ቁስ በሦስት መልኮች ቀርበዋል፡፡ በድንጋይ ላይ፣ በብራና ላይና በወረቀት ላይ፡፡
- የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፡- በድንጋይ ላይ የተጻፉት የግእዝ ሥነ ጽሑፎች በአኩስም አካባቢ የተገኙትንና የነገሥታቱን የጦርነት ታሪኮችንና ሌሎች ዘገባዎችን የያዙትን ጽሑፎች ይመለከታል፡፡ የተገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ከአራተኛው መክዘ(ቅልክ) እስከ 8ኛው መክዘ(ድልክ) የሚደርሱ ናቸው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ጥንታዊው የሚባለው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በመጣራ ኤርትራ በሐውልቲ የተገኘው(5ኛው መክዘ ቅልክ) ጽሑፍ ነው፡፡
‹‹ዝ ሐውልት ዘአገበረ
አገዘ ለአበዊሁ ወሰ
ሐበ ሙሓዛተ አውዐ
አለፈነ ወጸበለነ›› የሚለው ነው፡፡
እነዚህ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች አብዛኞቹ ዘገባዎችና ታሪኮች ሃይማኖታውያን አይደሉም፡፡

