ቴዎድሮስ ካሣሁንን በአካል አላውቀውም፤ በዘፈንና በጭፈራ በእውነት ተደሳች መሆን ካቃተኝ ቆይቷል፤ ከ ኅዳር 1967 ጀምሮ ነው የቆረቆረኝ፤ ይህ ሰው እንደሰውና እንደ ኢትዮጲያዊ በየጊዜው የሚደርስበትን ወደ ግፍ የሚጠጋ በደል ስመለከት ያው የለመድነው ምቀኝነት ነው እያልሁ ሳልፈው ቆየሁ፤ ግን በደሉ አላቆም አለ፤ ማንም ሊደርስለት አለመቻሉ ይበልጥ ያሳዝናል፣ በእሱ ላይ ተከታታይ የደረሰበት በደል የሕግ ያለህ የሚያሰኝ ነው፤ በቴዎድሮስ ካሣሁን ላይ በተቀነባበረ መንገድ የሚፈፀመው ማሰቃየት ማንንም ሰው የሚያሳስብ ነው፤ ምክንያቱ ምንድን ነው? በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
በቴዎድሮስ ላይ ከባድ ተንኮል ሲፈጸምበት የሰማሁት በመጀመሪያ ዛሬ በስደት ላይ ባለው « አዲስ ነገር» የሚባል ጋዜጣ ላይ ነበር፤ ጋዜጣው ቴዎድሮስ በሙያው ያገኘውን መልካም ስም በሰፊው ጥላሸት ቀብቶት ነበር፤ በጣም ሰፊ የሆነ ሀተታ በቴዎድሮስ ዘፈኖች ላይ በማቅረባቸው ምን ያህል አንገብጋቢ የአገር ጉዳይ አግኝተውበት ይሆን ብዬ አነበብሁት፣ ምንም ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ አላገኘሁበትም፤ በዘፈኖቹ ላይ በተደረገው ሂስም ከጋዜጠኞቹ መሀከል የሙዚቃ ሙያ ባለቤት እንዳለ ብጠይቅም ጋዜጣው ባለሙያ እንደሌለውና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ባለሙያ ማማከራቸውን ነገሩኝ፣ ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልግ ባለሙያ፣ ባለሙያ አይባልም፣ እንኳን በሙያው በራሱም አይተማመንም ማለት ነው፤ በዚህ በራሱ በማይተማመን ሰው ምስክርነት ላይ በተመሰረተ ረጅም ነቀፌታ ቴዎድሮስን ደበደቡት፤
ሁለተኛው የቴዎድሮስ ጣጣ በመኪና ሰው ገጭቷል ተብሎ መከሰሱ ነው፤ በሌሊት፣ በጨለማ ነው፤ ቴዎድሮስ እንደሚለው «እኔ ወደአገሬ የገባሁት ሰውዬው ሞተ በተባለበት ቀን ማግስት እንደሆነ ቪዛዬ ያረጋግጣል፣» (ነጋድራስ መስከረም 30/2001 ዓ.ም. ) በኋላም ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የተገኘው መረጃ ይህንኑ የሚያረጋግጥ እንደነበረ ተነግሮአል፤ በዚሁ በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ የሚከተሉት መረጃዎች ተጠቅሰዋል ፦




